አፍሮዳይት
ሳሙኤል በለጠ(ባማ)
የነፍስን ቅርጽ እያሰበ ቁዛሜውን ቀጠለ ክብ ፣ አራት ማዕዘን ፣ ሞላላ ፣ አባጣ ፣ ጎባጣ ምንድናት ? አለ
እስከዛሬ ቀሚሳቸውን ገልቦ ላባቸው ላይ በልቡ የተንሳፈፈባቸውን ሴቶች አሰበ ፥ አሃ እንደውም ወንድ ነፍስ የለውም የሚል ክብ ሐሳብ ሠራ በክብቦሹ ይጦዛል ። የጥዋት ፀሐይ ማንም ሳያያት ከተቀመጠበት ዲንጋይ ሥር ፈቀቅ ብላ ተቀምጣለች የብርሐኗን ጨረር ስታሰፋው ወደ ሠማይ ራቀች ፥ ትላንት ሥዕል ሊስል ቢቀመጥ ሸራው ከፊት ምስሏ ከኋላ ሆነበት ፥ አማተበ እንዴት በፍቅረኛሞች መኃል መጋረጃ ሊኖር ቻለ? ሊያውም ፊትና ኋላ አለ ። የምናብ ዓለሙን እያስታወሰ እንዴት ይቀፋል ? አለ።
እውቀት አንድ ነጥብ አለው ። አለማወቅ የተዘበራረቀ ነጥብ ነው ። ከተወላገደ ካካሉ ቀጥ ያለች ነፍሱን ለመፈለግ የቀለሞችን ነጥብ ማወቅ ፈለገ ግን ወንድ ውስጥ ነፍስ የለም ብሏል ፥ መንፈሳዊ ዓለሙን ሳይዳስስ ዓለማዊ ሕይወት ውስጥ ተደነቀረ ፥ ከጥላው ኋላ የምትከተለው ቅርጽ ዐልባዋን ነፍሱን እንዳይደፈጥጣት ፣ እንዳደፈጥጠው ይሳቀቃል ። ይፈልጋታል የእኔ ገነት እኔን ፣ ልቤን ፣ ቀለሜን ፣ እምነቴን ይዛለች ግን እኒህ በነፍስ ነው ። 'ሚታቀፉት አለው ራሱ ለራሱ ፥ ይህ ቡናማ ሐሳብ የልቡን አቶም ሰነጠቀው ፤ ሐሳቡ ሲሰክን ከስንጣቄው በጨለማ የተለወሰ ብርሐን ወጣ ፥
ከሚስለው ሥዕል ቀድሞ የፍትወት ቅርጽ አዕምሮው ላይ ይመጣል ፤ ገላዋ ሲነቃነቅ ቡርሹ ቀለም ይጠጣና በተንጋደደ ሸራው ላይ እግሯን ያጋድመዋል የእግር ጌጥ ይጨምርበታል ። ወዲያው ወደ ጉልበቷ ይሮጣል ። አጠፍ ያደርገውና ያዝለፈልፈዋል ። ፊቷ ወደ ማያየው ጀርባዋን መደሚያየው አድርጎ ይስላታል ። በባህር ውስጥ ደረቅ አድርጎ ፣ በብርሐን ውስጥ ጨለማ አድርጎ ፣ በውኃ ውስጥ እሳት አድርጎ ፣ ንፋስ ላይ ያዝናናታል ። ኋላ ላይ በሥጋ ይቆልፋታል... ነፍስ አሽከሯ ማነው ? አካል ! አካል ክፍያው ምንድነው ? ሞት አይደል ? ይላል በልቡ
ሥዕል ለመሳል ሥቃዩን እና ከደስታውን ይቀርባል ። ሁለቱ ነቁጦች አንድ ዓይነት ናፍቆትና ደስታ ያላቸው ሂደቶች ሲሆኑ የተለያዩ ቅርጾች ለውስጡ ይሰጡታል ። በሕይወትህ ወደ ነፍስህ ዘልቀው የሚገቡ፣ የዘላለም አካል የሚሆኑባቸው ቦታዎች አሉ። በሥዕል ሕይወት ውስጥ ሳይታሰብ አንድ ጊዜ የሐሴት ቦታዎችን ማግኘት አያስፈልግም ትላለህ ? አለኝ ቀና ብሎ
አንዳንድ አፍታዎች ዘለዓለማዊ ጥልቅ ማስታወስ ማዕዘኖች ዳር ያደርሱናል ። አይገርምም ? ለምን ሐሴትን ወድጄ ወሲብን ጠላሁ ? ፀሐይና መሬት እየተነካኩ ነው ። ሠማይ በጉያዋ የያዘውን ወርቃማ ብርሃን በተበሳሳው ጣራ ሥር ሲወረውረው በየግድግታው ጥግ የተዝረከረኩት ሥዕሎች ሕልም መስለው አሞጠሞጡ ፤ በነፍስ ውስጥ አንድ ሰው ለማስቀጠል ፣ ትኩስ ነፍስ ለማፍለቅ ምን ማድረግ አለብኝ ? ስል
ያቺ ልጅ አታምርም አትልም ? ስትል በውበቷ የሐሴትን ገጽ ለመግለጽ ነው ። በዕንባዋ የሳቅህን ነጭ ትዝታ ለመተዘት ነው ። ፈገግ አለ ሲጋራውን ለኮሶ ግጥጥ ብሎ ፈዞ ግድግዳ ተደግፎ ትኩዘ ልቡን በውሸት ሳቅ አጥቦ ዝም አለ :-
"ሰማህ መሌ"
"እ"
"እስቲ ያንን የጠነዘለ ሥጋ ያለውን ሥዕል እየው"
"አየሁት ሠማይ ላይ ነው ። ሐሴቱ ፀደይ ልብ ያላት አትመስልም ? ግን የአየር ስሜት ሳይሆን አይቀርም ? ዳርቻውን ከከበቡት የአበባ ቅርጫቶች በውፍረት ይበልጧታል ። አይበልጧትም ? "
እንደ መሳቅም እንደማዘንም ልቡ ተወዛወዘ በልክ የተከፈተው የሬጌ ሙዚቃ ይሰማል ። ከወጪ የሕጻናት የተስፋ መዝሙርና ጫጫታ የግድግዳውን በስቶ ሙዚቃውን ይከናነባል ። አየህ አልገባህም የዚህች ሴት ቀዳዳ ደም ፣ ነፍስ ፣ ቀለሙ ፣ ነጭ ፣ ጥቁሩ ፣ ቀዩ ፣ ሀምራዊው ፣ ክፍተቱ የሚሞላው በወሲቧ ታሪክ ነው ። የሚሰወርም ፣ የሚገለጥም ታሪክ የላትም ለዛነው የዓይኗ ዕንባ የከሳው ኦና መስመር ሆነ አካሏ አካሏን በላዋ ።
ደም ሥሬ እየራቀኝ መጣ ፥ ወሲብ ግን ክብደቱ
ለውይይታችን ግን የተፈጥሮ የመጀመሪያ አረንጓዴ ወርቅ ነው ። ይላል ሁል ጊዜ የእኔ ሴት ። ንጋት ወደ ቀን ታወርድልኛለች ፤ ትንፋሽ የሚጸነሱት መንታ ገጾች መልክ ሲይዙ ወሲብና ሥዕል ይሆናል ። ቅንጣት ዘላለም ይሰማኝ ይለኛል ፣ ይለኛል በጣም ደነገጥኩ የዝምታውን ጭጋግ ገፎ
"ውበት ከውበት ሲፈተግ ምን ይሆናል?"
"ሐሴት መሰለኝ"
"ነው።"
ቅዝቃዜ ከዐራቱም የአቅጣጫ ማዕዘናት ተሽከረከረብን በቅጽበት ወፍራም ዝናብ ወረደ ፤
ቤቱ አንገት በደዘዘ ጨለማ ተነቀሰ ፥ ከክፍሉ አንድ ጥግ በጨርቅ የተሸፈነ ብርሃን ተዝለግለግልጓል ። ጨርቅ ፣ እንጨት ፣ ትንሽ ብርሃን ፣ ጨለማ በዓይኔ ላይ ወደቀ ።
" ይሄ ሥዕል ያምራል ርዕሱም አፍሮዳይት ምን ማለት ነው ? "
"አፈ-ታሪክ ነው። አታውቀውም?"
"አዎ"
" የግርክ የፍቅር የወሲብ እርካታና የውበት ጣዖት ናት ብዙ አማልክትና ሰዎች ያፈቅሯት ነበር ፣ እርሷም ሰዎችንና አማልክትን አጠላም ልክ እንደኔዋ ኤልዳ አማልክት ያፈቅሯት ነበር ፡ ሰዎችም ያፈቅሯት ነበር ፤ ማን ይሆን እንዲህ ጣዖት አድርጎ የቀረጻት ? እኔን ብቻ ነበር የምታፈቅረው አማልዕክት ያፍቅሯት እንጂ አታፈቅራቸውም ሰዎች ይውደዷት አያቅፏትም ፣ በነጭ ጥርሷ ደረጃ ወደ ላይ ይወጣሉ፣ ይወርዳሉ ትስቅላቸዋለች ግን እኔን ብቻ ነው ። የምታቅፈው ከእኔ ጋር ብቻ ገነት አብረን የምንሄደው ፣ ዝም ብል ይሻለኛል በሥዕል- ዝም አልኩ እሷነቷን ቃሌ ሊቆጥራቸው አልቻለም ዝም ብል ይሻላል ። "
"አሁን የት ናት?"
"የለችም"
"ነፍሱ እርቃኗን ቆመች ምን ትደርብ ? ቀዝቃዛ አፍንጫውን ይነካካል ። ሲበርደኝ ወሲብ ነው የምደርበው ልጅ የተቀረጸውን ጡት ለመጥባት ሲልፈሰፈስ የሚሰማውን አይነት መራራ ሐዘን ተሰማው ጨለማ-ጨለማ ከውስጡ ሚወጣው ጅረት ክፍሉን አጥለቀለቀው ላይ ነፍሴ በጅረቱ ላይ ስትንሳፈፍ ሐዘኑ በላኝ ።"
"እኮ የት ሄደች?"
"በስዕሌና በልቤ ገድያታለሁ"
"ምን?"
"አዎ! አዎ ገድያታለሁ። ከፈለክ የጋረዷትን ሥዕሎች አንሳና እያት! ገድያታለሁ"
"ኤልዳን?"
"አዎ"
"ግን ለምን የልብ ምቷ አያቆምም?!" ትዝ ይለኛል ስዕሉን ሳስተውለው ከአካሏ ቀይ ደም አፈትልኮ ይሰማ ነበር
Comments
Post a Comment